ወጣቶች ‹‹የኢህአዴግ አባል አይደላችሁም›› ተብለው ከስልጠናው ተባረሩ

• ግማሽ ያህሉ ሰልጣኞች ህጻናት ናቸው

• ደህንነቶች ቤተሰቦቻቸውን እያስፈራሩ ነው!

• ‹‹ኢህአዴግም በ1997 ዓ.ም ገድሏል፡፡ ይህንንንም ለምን እንደታሪክ አንማርበትም?›› ሰልጣኞቹ

ኢህአዴግ አዲስ አበባ ውስጥ ለነዋሪዎች በየ ትምህርት ቤቱ በሚሰጠው ስልጠና ጥያቄ የጠየቁ ወጣቶች ‹‹የኢህአዴግ አባል አይደላችሁም›› ተብለው ከስልጠናው መባረራቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጸ፡፡ በስብሰባው ኢህአዴግ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ከሆነ ለምን ቀጥታ የቴሌቪዥን ክርክሮችን አያሳየንም? የምንሰለጥነው ስልጠና ለምርጫ ሲባል የተዘጋጀ ነው፣ የስራ እድል እንፈጥራለን የምትሉት ምርጫ ሲደርስ ነው፣ ባድመ በርካታ ሰው አልቆበት ለምን መፍትሄ አላገኘም? የሚሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች መነሳታቸውን ሰልጣኞቹ ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ጠንከር ያለ ጥያቄዎችን ያነሱ ሰልጣኞችን ደህንነቶች እንዳይሰበሰቡ የከለከሏቸው ሲሆን ቤት ድረስ በመሄድም ቤተሰቦቻቸውን እንዳስፈራሩባቸው ገልጸውልናል፡፡ አብዛኛው የስልጠና ክፍል ታሪክ ላይ ያተኮረ ሲሆን በተለይም አሰልጣኞቹ አጼ ምኒልክን ጨምሮ ያለፉት ስርዓቶች በኢትዮጵያ ለተፈጠሩት ችግሮች ተጠያቂ በማድረግ ኢህአዴግ ስህተት እንዳልሰራ መግለጻቸው ከሰልጣኞች ተቃውሞ ማስነሳቱ ታውቋል፡፡ ለአብነት ያህል አሰልጣኞቹ የቀደሙት ስርዓቶች ህዝብ የሚጨፈጭፉና ይህ ግፍ በኢህአዴግ ጊዜ የተቀረፈ አድርገው ሲያቀርቡ ‹‹ያለፉት ስርዓቶች ህዝብ ጨፍጭፈው ይሆናል፡፡ ይህን እንደታሪክ መማራችን አይከፋም፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግም ይገድላል፡፡ ለምሳሌ ኢህአዴግም በ1997 ዓ.ም ገድሏል፡፡ ይህንንንም ለምን እንደታሪክ አንማርበትም?›› ብሎ የጠየቀ ወጣት ‹‹የኢህአዴግ አባል አይደለህም፡፡›› ተብሎ በደህንነት ከስብሰባው መባረሩን ለዝግጅት ክፍላችን ገልጾአል፡፡

ወጣቱ ‹‹እኔ መጀመሪያ ስገባም የኢህአዴግ አባል እንዳልሆንኩ ያውቃሉ፡፡ ጥያቄ ሳነሳ ነው የኢህአዴግ አባል አይደለህም ብለው ያባረሩኝ፡፡ አሁንም ድረስ ጥያቄ ባለመጠየቃቸው እንጅ በርካቶች የኢህአዴግ አባል አይደሉም፡፡ ጥያቄ ያነሳ ሁሉ የኢህአዴግ አባል አይደለህም ተብሎ ይባረራል›› ሲል ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡ ወጣቱ ከስብሰባው ከተባረረ በኋላም ደህንነቶች ቤት ድረስ በመሄድ ‹‹አርፎ ቢቀመጥ ይሻላል›› ብለው ቤተሰቡን እንዳስፈራሩበት ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡ በተመሳሳይ ሌላ ወጣት ‹‹የሰማያዊ ፓርቲ አባል ነህ፡፡ ሰልጣኞቹን ለማነሳሳትና ሽብር ለመፍጠር ነው የመጣኸው፡፡›› ተብሎ ደህንነቶች ከስብሰባው እንዳባረሩት ገልጾአል፡፡

ከሰልጣኞቹ መካከል በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ፣ ስራ አጥ ወጣቶች፣ የቤት እመቤቶችና ሌሎችም እንደሚገኙ የታወቀ ሲሆን የተሰብሳቢውን ቁጥር ከፍ ብሎ እንዲታይ ህጻናትም እንዲሰበሰቡ መደረጋቸውን ከስልጠናው የተባረሩት ወጣቶች ገልጸዋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አባል ነህ ተብሎ የተባረረው ወጣት ‹‹ለማሟያ ተብለው የተሰበሰቡት ከግማሽ በላይ ተሰብሳቢዎች ከ12-15 አመት የሚሆኑ ህጻናት ናቸው፡፡ እነዚህ ወጣቶች የቀበሌ መታወቂያ እንኳን የላቸውም፡፡ ስልጠናው ለሚቀጥለው ምርጫ ቢሆንም ህጻናቱ ግን መምረጥ የሚችሉ አይደሉም፡፡›› ሲል ገልጾአል፡፡ ሌላኛው ከስብሰባው የተባረረው ወጣት በበኩሉ ‹‹እነዚህ ህጻናት ለማሟያ ካልሆነ በስተቀር የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ ምን አልባትም ከአሁኑ የኢህአዴግ አባል ሆነው እንዲዘልቁ ለማድረግም ይሆናል›› ብሏል፡፡

ምንም እንኳ ጠንከር ጥያቄዎች የሚነሱ ቢሆንም አሰልጣኞቹ የኢህአዴግን አስተሳሰብ ለመጫን እንጅ መልስ አይሰጡም ያሉት ሰልጣኞቹ ጠዋት የተጠየቀን ጥያቄ ወዲያውኑ ከመመለስ ይልቅ ከሰዓት አሊያም ነገ እየተባለ ሳይመለስ እንደሚቀር ገልጸዋል፡፡ በየ ትምህርት ቤቱ ‹‹ለኢህአዴግ አባልት ነው የሚሰጠው›› የተባለው ስልጠና 10 ቀናትን የሚፈጅ ሲሆን ለተሰብሳቢዎቹ በቀን 70 ብር አበል እንደሚሰጥም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ምንጭ ነገረ ኢትዮጵያ

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s