ሠራዊቱ የህዝብ ወገንተኛነቱን የሚያስመሰክርበት ግዜ እየመጣ ነው

August 3, 2014

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የቀደመው ትውልድ ከቱርክ ኤምፓየር፤ ከግብፅ እና ከደረቡሽ፤ ከጣሊያን ወራሪ፤ ከሶማሊያ ተስፋፊ ኃይል እና ከሌሎችም የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ተዋግቶ አገሪቷን ለአሁኑ ትውልድ ለማቆየት ትልቅ መስዋዕትነት ከፍሏል። በተለይ ነፍጥ አንግቦ የተሠለፈው ኃይል የከፈለው የህይወት መሥዋዕትነት የሚረሳ አይደለም። አገራችን ኢትዮጵያ ለዛሬው ትውልድ የቆየችው ከራሱ ይልቅ ለአገርና ለወገን የሚያስብ ትውልድ በመኖሩ መሆኑ የሚያከራክረን ጉዳይ አይሆንም።

የአገር መከላከያ ሠራዊት እና የአገር ደህንነት ኃይል የቆመው አገርን ከጥቃት ለመከላከል ነው። አገር በጠላት እጅ ወድቃ በወገን ላይ ስቃይ እንዳይደርስ፤ ህዝቡም አገር አልባ እንዳይሆን መጠበቅ የአገሪቷ የሠራዊትና የደህንነት ኃይል ዋና ተግባር ነበር። ህወሃት መራሹ መንግስት አገሪቷን ከተቆጣጠረ ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ ሥም የቆመው ሠራዊት እና የደህንነት ኃይል ተግባሩ ሌላ ሁኗል።

በዚህ ዘመን ሠራዊቱና የደህንነት ኃይሉ የአገርን ብሄራዊ ደህንነት የሚጠብቅ ሳይሆን ህወሃት የተባለውን ዘረኛና ዘራፊውን ቡድን የሚጠብቅ ኃይል መሆንን እንዲመርጥ ሁኖ አገርን ከጠላት የመከላከል ተግባሩን ረስቷል። ይህን ኃይል የሚመሩትም ደማቸውንና አጥንታቸውን ቆጥረው ከአንድ መንደር/ጎሣ የተሰባሰቡ እና ካርታ ይዘው የቆሙበትን ሥፍራ እንኳን ለመለየት የማይችሉ መሃይማን መሆናቸው አገሪቷ ያለችበትን አደጋ ከሚያመላክቱ ምልክቶች መካከል አንዱ ነው። ህወሃቶች የደርግ ሠራዊት እያሉ ሊሳለቁበት የሚሞክሩት የቀድሞው የአገሪቷ መከላከያ ኃይል ሲመራ የነበረው አውሮፓና አሜሪካን ድረስ ተጉዘው በተማሩ፤ ማዕረጋቸውም የዓለም ዓቀፉን ደረጃ የጠበቀ፤ አገሪቷን ወክለው አደባባይ ቢወጡ የሚያኮሩ እንደነበረ የታወቀ ነው። የሹመታቸው መሠረትም ደምና አጥንት ሳይሆን እውቀታቸው፤ ችሎታቸውና ወታዳራዊ ብቃታቸው ነበረ።በህወሃት የሚመራውን ሠራዊትና የደህንነት ኃይል የሚመሩት ቡድኖች ከቀድሞዎቹ ሥርዓት የጦር መሪዎች ጋር ሲወዳደሩ የጫማቸውን ጠፍር እንኳ ለመፍታት የሚታጩ አይሆኑም።ግዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል እንደሚባለው ሆነና ጨካኞችና ነፍሰ ገዳዮች በወንበሩ ቁጭ ብለው የአገሪቷን ውድቀት እያፋጠኑት ይገኛሉ።

ዛሬ ህወሃቶች በወንበሩ ቁጭ ብለዋል። እነዚህ ከጭካኔ በቀር እንጥፍጣፊ የአገር ፍቅር የሌላቸው ቡድኖች አቋቋምን ያሉት ሠራዊትና የደህንነት ኃይልም አገሩንና ወገኑን ከመጠበቅ ይልቅ የገዛ ወገኑን የሚያሸበር ቡድን እንዲሆን ተደርጓል። ሠራዊቱ እና የደህንነት ኃይሉ ለአገርና ለትውልድ እንዲያስብ ሳይሆን የጥቂት ዘረኞችን ዕድሜ ለማራዘም ዘብ የቆመ ኃይል እንዲሆንም ሁኗል። ህወሃት እየፈጠረ ያለው ሠራዊትና የደህንነት ኃይል በጀግና ማዕረግ አገሩንና ህዝቡን ከጥቃት ተከላክሎ በህዝቡ ተከብሮና ተወዶ እንዲኖር ሳይሆን በጭካኔው ታውቆ እና የወገኑን ፍቅር አጥቶ በስነ ልቦና ቀውስ ውስጥ የሚኖርን ኃይል ነው። እንዲህም ሁኖ በመቀረፁ ግደል ሲባል ገስግሶ ሂዶ የገዛ ወገኑን ይገድላል። አፍርስ ሲባል ፈጥኖ በብዙ ድካምና ወጪ የተገነባውን የወገኑን መኖሪያ ቤት ያፈርሳል። እሠር ሲባል ህፃን ከአዛውንት ሳይለይ ያገኘውን ሁሉ ወደ ወይኒ ቤት ያግዛል። በእንዲህ ሁኔታ ከወገኑ ተለይቶ፤ በወገኑ ላይ ዘምቶ፤ ወገኑን ወግቶ፤ ወገኑን አሥሮና አሰቃይቶ ራሡም እንደገና በክፉ ድርጊቱ ታሥሮ እንዲኖር ሁኗል።

ህወሃት የፈጠራችሁ እና በአገር መከላከያ እና ደህንነት ኃይል ሥም ቁማችሁ በወገኖቻችሁ ላይ እንድትዘመቱ የተደረጋችሁ የሠራዊቱና የደህንነት ኃይሎች አድምጡ። አሁን አገራችን ባለችበት ሁኔታ ለኢትዮጵያና ለህዝቧ ዋነኛው ጠላት ህወሃት ነው። ህወሃት የዘረኞችና የዘራፊዎች ስብሰብ ነው። የዘረኝነታቸው መገለጫ ብዙ ነው። የሚያዙህ ጄኔራል ተብየዎች ደማቸውን ቆጥረው የተጫኑብህ መሆናቸውን ተመለከት። እነዚህ ጄኔራሎች አገሪቷን ከተቆጣጠሩ ዘመን ጀምሮ ያካበቱትን የሃብት ብዛት ተመልከት። ሁሉም በሚሊዮን የሚቆጠር ሃብት ባለቤት ናቸው። ልጆቻቸው በአውሮፓና በአሜሪካን ይማራሉ። ሚስቶቻቸው አውሮፓና አሜሪካን እየሄዱ እንዲወልዱ ይደረጋል።ይሄን ለምን ያደርጋሉ ቢባል እየገዙ ያሉት አገር የራሳቸው አገር ስለመሆኗ ብርቱ ጥርጣሬ ስላላቸው ነው። ህዝቧንም እንደ ወገኖቻቸው ለማየት ሥር የሰደደ ጥላቻማላቸው። አንተ እና ወገኖችህ ግን ከሙታን ትንሽ ከፍ ብላችሁ፤ ከሚኖሩት እገር ሥር ተረግጣችሁ የህወሃቶች አኗኗሪ ሁናችሁ የመከራውን ዘመን ትቆጥራላችሁ። በድህነት የሚወቅሯችሁ እንሷቸው ይሄና አስባችሁ፤ ያንን ተናገረችሁ እያሉ በዓለም ላይ በተከለከለ የቶርቸር ዓይነት እንድትሰቃዩ ትደረጋላችሁ። ይህ የጠላት ተግባር ነው።አሁን ባለንበት ዘመንም የኢትጵያ ዋነኛው ጠላት ህወሃት መሆኑን ያለምንም ጥርጣሬ ማመን ይኖርባችኋል።

ህወሃትን ጠላት የሚያድረገው ምንድ ነው ?

ህወሃቶች ወደ ስልጣን ከመጡ ዘመን ጀምሮ ሁለት ሚሊዮን አማራ ጠፍቷል። ይሄ ሁሉ አማራ የት እንደገባ ህወሃት እስከ አሁን አልተናገረም። ይሄ ዘረኛ ቡድን አገሪቷን ከተቆጣጠረ ዘመን ጀምሮ በዜጎች መካከል ሊኖር የሚገባው መተማመን ጠፍቷል። በዚህም ምክንያት ዜጎች ከኖሩበት ሥፍራ እየተነቀሉ ሜዳ ላይ እንዲወድቁ ሁኗል። ይሄ ዘራፊ ቡድን አገሪቷን ከተቆጣጠረ ግዜ ጀምሮ ከአገሪቷ ውስጥ በስምንት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተዘርፎ በውጪ አገራት ባንኮች ውስጥ ተደብቋል። ይህ ቡድን ስልጣኑን ከተቆጣጠረ ዘመን ጀምሮ ከአገሪቷ በሚሰደዱ ምሁራን፤ ጋዜጠኞች፤ የኃይማኖት አባቶች እና በሌሎች ዜጎች ቁጥር ኢትዮጵያን የሚያክል አልተገኘም። ህወሃት የተባለው ዘረኛ እና ዘራፊ ቡድን አገሪቷን ከተቆጣጠረ በኋላ አባቶች በደምና አጥንታቸው ያቆዩት ድንበር እየፈረሰ እና ኢትዮጵያዊያን እየተፈናቀሉ ሜዳ ላይ ተጥለው መሬቱ ለባእዳን እየተሰጠ ነው። ይሄ ቡድን አገሪቷን ከተቆጣጠረ ዘመን ጀምሮ ድሃ ሜዳ ላይ ተጥሎ የድሃውን መሬት ህወሃቶች እየነጠቁ ባለሃብት ነን ብለዋል። ይሄ ቡድን አገሪቷን ከተቆጣጠረ ዘመን ጀምሮ ሃሳብን በነፃ መግለፅ አሸባሪነት ሁኗል። ህወሃትን መንቀፍ በሞት የሚያሰቀጣ ወንጀል እስከመሆን ደርሷል። ኢትዮጵያ ይህን በሚመስለው ጠላት እጅ ተይዛለች።

ኢትዮጵያን ከዚህ ጠላት እጅ ለማላቀቅ የሠራዊቱና የአገር ደህንነት ኃይሉ ከፍተኛ ሚና መጫወት አለበት። ከህወሃት የበለጠ ጠላት ኢትዮጵያ የላትም፤ በታሪኳም እንዲህ ዓይነት ጠላት አይታ አታውቅም። ይህን ጠላት ወደ ከርሰ መቃብሩ የሚከት የለውጥ ባቡር እየገሰገሰ ነው። ይሄን የለወጥ ባቡር ፈፅሞ ማቆም አይቻልም። ህወሃቶች የለውጡ ባቡር በፍጥነት እየገሰገሰ እንደሆነ እያዩት ነው። በዚህም አንዳንዶቹ የዘረፉትን ሃብት ይዘው እየሸሹ ነው። ሌሎቹም የሚያደርጉትን አጥተው በዜጎች ላይ በስቃይ ላይ ስቃይ እያበዙ ነው። የሠራዊቱና የደህንነቱ ኃይል የኢትዮጵያዊያን ጠላት መሆንን ከመረጡ ዘረኞች ጎራ ራሱን ለይቶ የህዝብ ልጅ፤ የአገር ጥላ ከለላ መሆኑን አሁኑኑ ማሳየት መጀመር ይጠበቅበታል። የአገር መከላከያ አባል ስትሆን አገርህን ከጠላት ለመከላከል እንጂ ከጠላት ጋር አብረህ የገዛ ወገንህን ስቃይ ለማብዛት አይደለም። ከጠላት ጋር መወገንን ከመረጥክ ግን የተነሳው የለውጥ ባቡር አንተንም ጨፍልቆ እና ታሪክህን ከዘረኞችና ከዘራፊዎች ጎራ ፅፎ እንደሚያልፍ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ አይኑርህ።

የእኛ እምነት ግን ከህወሃቶች ጎን ቁመህ ወንድሞችህን ትወጋለህ የሚል አይደለም። ህወሃቶች ለአንት ወንድምም ጋሻም መከታም የሚሆኑ አይደሉም። በአሁን ሠዓት የህወሃቶች ጭንቀት የዘረፉትን ሃብት የሚያሸሹበትን ሥፍራ የማግኘት ነው እንጂ የአንተ ደህንነት አይደለም። ህወሃቶችን እንቅልፍ የሚነሳቸው የሠሯቸው ትላልቅ ህንፃዎች ፍፃሜ እንጂ የኢትዮጵያዊያኑ በሠላም የመኖር ጉዳይ አይደለም። ህወሃቶች የሚሞቱለትም ሆነ የሚኖሩለት አንድ እና አንድ ምክንያት ዘርፈው ያካባቱት ሃብት እንጂ ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንዳልሆነች የታወቀ ነው። አንተ የሠራዊቱ አባል ግን የእነዚህን ዘረኞችና ዘራፊ ህወሃቶችን እድሜ ለማራዘም የምትሞተውና የምትገድለው ለምንድ ነው? የእነርሱን እድሜ ለማራዘም ብለህ ብትሞት ለህወሃቶች ወግኖ ኢትዮጵያዊያንን ሲወጋ ሞተ ተብለህ መሳለቂያ ሆነህ መቅረትህን አታውቅምን ?

እኛ ግን እንዲህ እንልሃለን ለአገርህ መሞት ክብር ነው። ለአገር መሞት ማለትም በዚያች አገር ውስጥ ለፍትህ፤ ለህግ የበላይነት፤ ለነፃነት፤ ለእኩልነት እና ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ራስን አሳልፎ መስጠት ማለት ነው።በዚህ ሞትህ ማንም ማንንም ሳይጫን፤ ማንም ማንንም ሳይሸከም መኖር የሚቻልባት አገር ተፈጥራ እኩልነት ሲሰፍን የአንት ስም በአገሪቷ እስከ ዘላለሙ ሲታወስ ይኖራል። ልጆችህና ልጅ ልጆችህ በአንተ ሥራ ኮርተውና አንገታቸውን ቀና አድርገው የሚሄዱ ይሆናሉ። ለዚህ ዘላቂ ክብር ብለህ ብትሞት ሞትህ የክብር ሞት ይሆናል። የሣሞራንና የጓደኞቹን የሥልጣን ጥም ለማርካት ብለህ ብትገልና ብትሞት ግን አሟሟትህ ከንቱ ይሆናል። ለነፃነት፤ ለእኩልነት እና ለህግ የበላይነት ብለው የተነሱ ነፁሃን ዜጎችን ለመግደል የታጠከውን ነፍጥ ብታነሳ ፍፃሜህ ከንቱ ሁኖ እንደሚቀር አትጠራጠር። የምትሞትለትም ሆነ የምትኖርለት ዋናው ቁም ነገር ሊሆን የሚገባው በህወሃቶች የተጣመመውን ፍትህ ለማቃናት፤ ወገኖችህና አንተ የተነጠቃችሁትን ነፃነት ለመቀዳጀት፤ እውነተኛ ዴሞክራሲዊ ሥርዓት በአገርህ እንዲሠፍን፤ ጥቂት ዘረኞች ብዙሃኑን ተጭነው፤ ብዙሃኑም እነዚህ ጥቂት ዘረኞችን ተሸክመው የሚኖሩበት ሥርዓት እንዲያበቃ ሊሆን ይገባዋል። ለእነዚህ ድንቅ ሃሳቦች ብለህ ብትሰዋ መስዋዕትነትህ የጀግና መሥዋዕትነት ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱ መሰዋዕትነት ለአገርና ለወገን የሚሰጥ ውድ እና ታላቅ ስጦታ ነው። ይሄን ውድ እና ታላቅ ስጦታ የሰጠ ደግሞ በታሪክ ማህደራት ውስጥ ስሙ ለዘላለም ሲታወስ ይኖራልና የለወጡን ባቡር እንድትሳፈር እንመክርሃለን።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s