የሚፈራው መጣ!!!

ማጣፊያው ሳያጥር ቅድሚያ ለእምዬ ኢትዮጵያ!! (ርዕሰ አንቀጽ)

prayer

August 5, 2013 09:14 am By  1 Comment
ኢትዮጵያችን ታማለች። ኢትዮጵያችን ተወጣጥራለች። ኢትዮጵያችን በአደገኛ መርዝ ተበክላለች። ኢትዮጵያችን ውስጧ ነፍሯል። ኢትዮጵያችን እየቃተተች ነው። ቆዳዋ ሳስቷል። የሚሰማትና የሚደርስላት ስላጣች የያዘችውን ይዛ ልትነጉድ ከጫፍ ላይ ነች። እናም ቅድሚያ ለመቀመጫ፤ ቅድሚያ ለእምዬ ኢትዮጵያ!! ማጣፊያው ሳያጥር ሁሉም መንገዱን ይመርምር!!

ኢትዮጵያ በጭንቀት ጣር ውስጥ ስለመገኘቷ ማብራሪያ የሚጠይቁ ዜጎች ያሉ አይመስለንም። ምናልባት ሳያውቁ እየተፈረደባቸው ያሉ ህጻናት ካልሆኑ በስተቀር፤ ችግር ፈጣሪውም፣ የችግሩ ሁሉ ሰላባ የሆነው ህዝብ፤ ሁሉም ከበቂ በላይ መረጃ አላቸው። ኢትዮጵያ ህመሟ ወደ “ሚድን ካንሰርነት” መቀየር የሚችል ስለመሆኑ ዜጎች ያለ “ሰበር ዜና” ይረዱታል።

የሚድን ስንል በቀላል አገላለጽ ችግር ፈጣሪው ኢህአዴግ፣ የኢህአዴግ ሾፌር ህወሃት፣ የህወሃት አገልጋዮች፣ በህወሃት የበላይነት ከበሮ የሚደልቁ ወንድምና እህቶች፣ ጊዜ የሚያረጅና እራፊ ሆኖ የሚያልፍ የማይመስላቸው የትዕቢት ውጤቶች፣ ይህንን ሁሉ ታግለን “ዴሞክራሲ እናወርዳለን” የሚሉ ወገኖች በልዩነት “አንድ” በመሆን ኢትዮጵያን ለህዝብ ውሳኔ አሳልፈው መስጠት ሲችሉ ነው።

“የጦርነት አባቱ እኔ ነኝ፣ እኔ ከሌለሁ አገር ትከስማለች፣ ኢትዮጵያ በደም ትታጠባለች፣ እኔ ወደ ሰሜን እሸሻለሁ … ” እያለ የቀን ቅዠት ቃዥቶ እወክላቸዋለሁ የሚላቸውን ወገኖች በስጋት ጤና እየነሳ ያለው ኢህአዴግ፣ በተለይም ህወሃት ቀን በጨመረ ቁጥር በእሳት እየተጫወተ ነውና የራሱ ደጋፊዎች ወደ ሰላም መንገድ እንዲመጣ ሊያስገድዱት ይገባል።

የተናፈናቀሉ፣ ከስራ የተባረሩ፣ በቂም ከነቤተሰቦቻቸው ለልመና የታደረጉ፣ ቤተሰቦቻቸው የታሰሩባቸው፣ የተገደሉባቸው፣ በዘራቸው ሳቢያ የመከራ አረም እንዲመገቡ የተደረጉ፣ የተዘረፉና እየተዘረፉ ያሉ ዜጎች፣ በብሄር እየተተመኑ ከተወዳዳሪነት የተገለሉ ኢትዮጵያዊያኖች፣ እምነታችን ተነካብን የሚሉ የኢትዮጵያ ቤተሰቦች … ብዙ ማለት ይቻላል፤ ሁሉም አምርረዋል። ቁጣቸው ከጫፍ ደርሷል። ደጋግመን እንደምንለው ዛሬ ጊዜው የእርቅና ሰላም የማውረድ በመሆኑ ለሚሰሙ ወገኖች “ቅድሚያ ለእምዬ ኢትዮጵያ” የሚል አደራ እናስተላልፋለን። በተለይ በ1997 የምርጫ ወቅት ኢትዮጵያን ወደተሻለ ቦታ ሊያደርሳት የሚችለውን ወርቃማ ዕድል ከእጁ እንዲያፈተልክ ያደረገው ኢህአዴግ አሁንም ይህንን ወቅት ጊዜው ሳያልፍና ሁኔታዎች ወደነበሩበት የማይመለሱበት ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት ሊጠቀምበት ይገባል፡፡ አገር ካለፈች በኋላ ልማት፣ ህዳሴ፣ ውዳሴ፣ ግድብ፣ … አንዳቸውም አይኖሩም!

አንድ ዓመት ያስቆጠረው የሙስሊሞች ጥያቄ በወጉ ካልተያዘ መከራው እንደሚሰፋ አስቀድመን ለፍልፈናል። ከቀን ወደ ቀን እየገፋ የሄደው ተቃውሞ በወጉ ተመርምሮ እናታችን ኢትዮጵያን ለአደጋ በማይጥል መልኩ እልባት እንዲሰጠው አሁንም ደግምን ደጋግመን እናሳስባለን። በግርግር ሳይሆን በማስተዋል “ቅድመ ሁኔታ” ያስቀመጠ የሰላም መንገድ እንዲፈለግ ያገባናል የሚሉ ሁሉ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲጀምሩ በቀጣዩ ትውልድ ስም እንጠይቃለን። የ“ድምጻችን ይሰማ” ጥያቄ ድምጽ የማሰማትና የመብት ጥያቄ እስከሆነ በአግባቡ ይመለስ፡፡ ከዚህ ሌላ ጥያቄ ካላቸው ለህዝብ ይፋ ያድርጉ፡፡ የሙስሊሙ ኅብረተሰብ ከኢህአዴግ ጋር ላለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት ሰላማዊ ግንኙነት እንደነበረው ግልጽ ነው – ባለፉት ሥርዓቶች ባልታየ መልኩ በተለያዩ ከተሞች የበርካታ መስጊዶች መሠራትም ሆነ የአምልኮ ሥርዓታቸው መከበር ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ታዲያ አሁን የሃይማኖትና የመብት ይከበር ጥያቄያቸው የሥልጣንና ፖለቲካዊ ይዘት ያለው መስሎ ለምን ቀረበ? እስካሁንስ ለምን መፍትሔ ሊገኝለት አልችል አለ?

የሚፈሩና የሚከበሩ የፖለቲካ መሪዎች የሉንም። የምንወዳቸውና ሲናገሩ የምናዳምጣቸው የሃይማኖት መሪዎች ባለቤት መሆን አልቻልንም። ለተግሳጽ አደባባይ የሚወጣ ሽማግሌ የለንም። ከውጪም ከውስጥም  መተማመን ጠፍቷል። የክስረታችን ብዛት ባዶ አስቀርቶናል። የቀረን አንድ ነገር ቢኖር እማማችን ኢትዮጵያ፣ እያቃተተች ያለችው አገራችን ናት። ይህችኑ ቤታችንን ተረባርበን ማዳን ካልቻልን ሁሉም ያከትምና ላናገግም እናዝናለን። በርካታ ንጹሃንን እናጣለን!! እባክችሁ የህወሃት ሰዎች ሁሉንም ጎን እዩት። ወደ ልባችሁ በመመለስ የእርቅን መንገድ ፈልጉ። በውል እንደምትረዱት ነገሮች ሁሉ መልካቸውን የሚቀይሩበት ወቅት ተቃርቧል። እባካችሁን የኢህአዴግ ሰዎች ያለፍርሃቻ እርቅ በቤታችሁ እንዲታወጅ መስዋዕት ሁኑ። ዝምታችሁን ቅበሩና ኢትዮጵያንና ወገኖቻችሁን፣ ልጆቻችሁን፣ ቤተሰቦቻችሁን አድኑ። የህዝብን ጥያቄ መልሱ!

በወጪ አገርም ሆነ በአገር ቤት የምትኖሩ የእርቅ ሃሳብ ባሪያዎች፣ ኢትዮጵያን ለመታደግ የምትፈልጉ ወገኖች ኢትዮጵያ ላይ ከየአቅጣጫው የተረጨውን የጥላቻ መርዝ ለመግፈፍ ተነሱ። ኢትዮጵያን ለማዳን ይሉኝታና ማመንታት ዋጋ የላቸውምና ከተጋረዳችሁበት መጋረጃ ውጡ። የሃይማኖት አባቶች እባካችሁን ንስሃ በመግባትና ህዝቡንም ንስሃ በማስገባት የሰላም አባት ሁኑ። ቀሪ ዘመናችሁን በደስታ ሰክራችሁ ትኖሩ ዘንድ ያጎደፋችሁትን ስማችሁን አድሱ። አገር ከሌለ መብትም ሆነ ዴሞክራሲ፣ ነጻነት አይኖሩም፡፡ አገር ከሌለ ድምጽ አሰሚም ሆነ ድምጽ ሰሚ የለም፡፡ አገር ከሌለ ልማትና ብልጽግና አለመኖር ብቻ ሳይሆን ተደረገ የተባለውም ወዳለመኖር ይቀየራል፤ አገር ከሌለ ማንነት ይቀራል፤ ይህንን ማስጠንቀቅና የዕርቅ ሃሳብ ማቅረብ ዕልቂት ናፋቂነት አይደለም።

ልብ ያለው ያስተውል! ጆሮ ያለው ይስማ! ኢትዮጵያ እየቃተተች ነው። ማጣፊያው ሳያጥር ቅድሚያ ለእምዬ ኢትዮጵያ!!

 

source/http://www.goolgule.com

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s